አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የድህረ-ማላቦ አጠቃላይ የአፍሪካ ግብርና ልማት ፕሮግራም (ሲኤኤዲፒ) የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በኡጋንዳ ካምፓላ እየተካሄደ ነው፡፡
ጉባዔው ”ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የጋራ ብልጽግና ሁሉን አቀፍ የግብርና ሥርዓት ሽግግርን ማራመድ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
ጉባዔው ከማላቦ በኋላ ማለትም ከፈረንጆች 2026 እስከ 2035 ያለውን የአፍሪካ የግብርና ሥርዓት አጀንዳ በመቅረጽ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተሳተፉበት ጉባዔው÷የአፍሪካ መሪዎችን ጨምሮ የልማት አጋሮች የካምፓላ ሲኤኤዲፒ ረቂቅና የ10 ዓመት ስትራቴጂ እንዲሁም የድርጊት መርሐ ግብር እንዲደግፉ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
እነዚህ ወሳኝ ሰነዶች በማላቦ ስምምነት (2014-2025) ስኬቶች እና የሚወሰዱ እርምቶችን በመመልከት በአህጉሪቱ የግብርና ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ ያለሙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በጉባዔው የአፍሪካ ህብረት የልህቀት ማዕከላት ለአሳ ሃብት፣ የውሃ ሃብትና ብዝሃ ሕይወት በማቋቋምና ከዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሁሉን አቀፍ ልማት እንዲኖር የመንግስት ባለድርሻ አካላት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ላይ ትኩረት በሚደረግበት ላይ እንደሚመክር ተጠቅሷል፡፡