የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል ወደ ልማት ባልገቡ ባለሃብቶች ላይ ርምጃ ተወሰደ

By Melaku Gedif

January 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል በተለያዩ የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሰማራት መሬት ወስደው ወደ ልማት ያልገቡ 24 ባለሃብቶች ላይ ርምጃ ተወሰደ፡፡

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የመሬትና ማዕድን ቢሮ  ሃላፊ አቶ ካልአዩ ገብረህይወት እንዳሉት÷ ርምጃው የተሰጣቸውን መሬት ከማስመለስ ጀምሮ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት የደረሰ ነው፡፡

ከባለሃብቶቹ መካከል አራቱ ምንም ዓይነት ልማት ያልጀመሩ እና ለሌላ አከራይተው በመገኘታቸው የወሰዱትን መሬት ሙሉ በሙሉ እንዲመልሱ መደረጉን ተናግረዋል።

ለባለሃብቶቹ የተሰጣቸው 500 ሄክታር መሬት ወደ መንግስት እንዲመለስ መደረጉን ነው ሃላፊው ያስታወቁት።

በሌሎች 20 ባለሃብቶች ላይ ደግሞ ለ6 ወራት የሚቆይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አቶ ካልአዩ ለኢዜአ ገልጸዋል።