የሀገር ውስጥ ዜና

አመራሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሊሰራ ይገባል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

By Mikias Ayele

January 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አመራሩ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ሊሰራ ይገባል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰን አሳሰቡ፡፡

በክልሉ ላለፉት አራት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የከፍተኛ አመራሮች ወቅታዊ የውይይት መድረክ ሲጠናቀቅ ርዕሰ መስተዳደሩ በሰጡት የሥራ መመሪያ፤ አመራሩ የዜጎችን ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ አጀንዳዎች ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በየደረጃው የሚገኘው አመራር ለህዝቡ ሁለንተናዊ ለውጥ መትጋት እንዳለበት ገልጸው÷ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።

አመራሩ በክልሉ የተገኘውን ሰላም እና ልማት ከማህረሰቡ ጋር በመቀናጀት በዘላቂነት በማጽናት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ኤኒሸቲቮች ውጤታማ እንዲሆኑ አመራሩ ግንባር ቀደም ሚናውን መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።

ከመንግሥታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ጋር ተያይዞ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ለህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉን የተፈጥሮ ፀጋዎች በሚገባ በማልማት ከዘርፉ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአመራሩ ተቀዳሚ አጀንዳ መሆን አለበት ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡