አዲስ አበባ፣ ጥር 01፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲጋላ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታውቋል፡፡
በተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለፁት÷ የአዲጋላ ማከፋፈያ ጣቢያ የኤክስፖርት ጣቢያ ከመሆኑ ባለፈ ወደ ጅቡቲ ለተዘረጋው የውሃ መስመር አስተማማኝ ኤሌክትሪክ እያቀረበ ይገኛል።
ተቋሙ ለሚያከናውነው የሃይል ሽያጭና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ ለተመሰረተው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ ጣቢያው አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የማከፋፈያ ጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ሳሙኤል በበኩላቸው÷ ጣቢያው የተገነባው ኢትዮጵያ በምስራቁ በኩል ከጎረቤት ጅቡቲ ጋር ለሚኖራት የሃይል ኤክስፖርት ማሳለጫ ታስቦ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
25 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመርና 74 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው 4 ሪአክተሮች እንዲሁም በ33 ኪሎ ቮልት አምስት ወጪ መስመሮች ጠቁመዋል፡፡
ወጪ መስመሮቹም ለአዲጋላ፣ ለአይሻ፣ ለደወሌ እና ለአርዌ ከተሞች እንዲሁም ለኢትዮ- ጅቡቲ የባቡርና ለጅቡቲ የውሃ መስመሮች አስተማማኝ ኤሌክትሪክ እያቀረቡ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በጣቢያው የሚገኙት አራቱ ሪአክተሮች የቮልቴጅ መዋዠቅ ችግር እንዳይፈጠር በማድረግ የተመጠነ እና ያልተቆራረጠ ሃይል እንዲቀርብ ያስችላሉ ማለታቸውንም የተቋሙ መረጃ ያመላክታል፡፡