Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዜጎች በአንጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ውስጥ በንቃት የመሳተፋቸው አስፈላጊነት…

በሀገራዊ ምከክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

ነገር ግን ዜጎች እና ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ውስጥ በንቃት መሳተፋችው ለምን አስፈለገ? የትኞቹን ውጤቶች እንዲያመጣስ ይጠበቃል?

👉 አካታች የሆነ ውሳኔ ሰጪነትን ለማረጋገጥ

በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ ከዜጎች የሚሰበሰቡ አጀንዳዎች ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

በሂደቱ ሁላችንም ሀሳባችንን ለማቅረብ በንቃት መሳተፋችን ሂደቱን ስኬታማ ከማድረጉም በላይ በሀገራችን ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለመጫወት በር ይከፍትልናል፡፡

👉 የዜጎችን ጥያቄዎች ለመረዳት

በሀገራዊ ምክከር ሂደት ውስጥ በዜጎች እና ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡ የአጀንዳ ሀሳቦች ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸውን ስሜት እና ፍላጎት እንዲያንፀባርቁ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለተፈጠሩ ችግሮች የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ መንገድ ከፋች ነው፡፡

👉 ድምፃቸው ያልተሰማ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለማስተናገድ

የሀገራዊ ምክክር በተለያዩ አጋጣሚዎች በሀገራችን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር ውስጥ ድምፃቸው ጎልቶ ያልተሰማ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሀሳቦችን ለማስተጋባት መደላድል ይፈጥራል፡፡ እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለተካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸው ሀሳባቸውን ማቅረባቸው በሀገራችን የዲሞክራሲ ልምምድ ላይ በጎ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡

👉 ዜጋ-ተኮር መፍትሔዎችን ለማመንጨት

የሀገራዊ ምክክር ሂደት ባለቤት ህዝብ እንደመሆኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ዜጎች ሀሳቦቻቸውን በቀጥታም ይሁን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሲያቀርቡ በሂደቱ ሊኖራቸው የሚገባው የባለቤትነት መብት እንዲረጋገጥ መንገዱን ይጠርግላቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በሚቀርቡ የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ዜጎች የጉዳዩ ማዕከል ሆነው በሀገራዊ ምክክሩ ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በጋራ ማመንጨት ይችላሉ፡፡

👉 መተማመንን እና ማህበራዊ ትስስርን ለመገንባት እና ለማደስ

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በእውነት እና በግልፅ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን ማቅረባቸው የጋራ መተማመንን ለመገንባት ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ በሂደቱም ሀሉም አካላት ካለፈው ተምረው ስለ ነገዋ የጋራ ሀገራቸው መክረው የማህበራዊ ውሎቻቸውን ያድሳሉ፡፡

በመሆኑም በመላው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራችን መፃኢ ተስፋ ላይ ጉልህ ሚና በሚኖረው በዚህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ተሳታፊ በመሆን ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በጋራ ማምጣት እንዲቻል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኮሚሽኑ በመደበኛ መልክ አጀንዳዎችን የሚሰበስብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እርስዎ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ ቢነሳልኝ የሚሉትን አጀንዳ/ዎች በቡድን ወይም በግል ከታች በተቀመጡት አድራሻዎች ማቅረብ እንደሚችሉም ተመላክቷል፡፡

የአጀንዳ ሃሳብዎትን፡-

👉 ከአሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ በሚገኘው የኮሚሽኑ ፅ/ቤት በፅሁፍ ማስገባት ፡፡

👉 በፖስታ ሳጥን ቁጥር፡ 32623 አዲስ አበባ

👉 በኢሜል፡ ethiopianndc@gmail.com

👉 በኮሚሽኑ ድረ-ገፅ፡ https://ethiondc.org.et መጠቀም ይችላሉ፡፡

Exit mobile version