ዓለምአቀፋዊ ዜና

በሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት እስከ 57 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ጉዳት አደረሰ

By Meseret Awoke

January 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ ደቡብ ካሊፎርኒያ ግዛት በምትገኘው ሎስ አንጀለስ የተከሰተው ሰደድ እሳት ከ52 እስከ 57 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ውድመት አድርሷል ተባለ፡፡

ሰደድ እሳቱ ከፍተኛ ነፋስ የቀላቀለ መሆኑን ተከትሎ አሁንም በፍጥነት እየተዛመተ ነው ተብሏል፡፡

እንደ ሲኤን ኤን ዘገባ በሰደድ እሳቱ ቢያንስ የአምስት ሰዎች ሕይዎት አልፏል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕንጻዎችም እየወደሙ ነው፡፡

ሬውተርስ የአሜሪካ የአየር ሁኔታ ትንበያ ተቋምን (አኩዌዘር) ጠቅሶ እንደዘገበው፥ ሰደድ እሳቱ ያደረሰው ጉዳት ከ52 እስከ 57 ቢሊየን ዶላር ይገመታል፡፡

ሰደድ እሳቱ ቶሎ በቁጥጥር ሥር ካልዋለ እና ተጨማሪ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ በዘመናዊ የካሊፎርኒያ ታሪክ ውስጥ በተቃጠሉት ሕንጻዎች ብዛትና በኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እጅግ የከፋው ሰደድ እሳት ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡