Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፌዴራል ሱፐርቪዥንና ድጋፍ ስራዎች የልማት ተደራሽነትን ያሰፋሉ – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ሱፐርቪዥንና ድጋፍ ስራዎች የልማት ተደራሽነትን በየአካባቢው በማስፋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

 

የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን አባላት በተለያዩ ክልሎች ያከናወኗቸውን የመስክ ምልከታዎች የሚመለከት የአፈጻጸም ግምገማ ሪፖርት መድረክ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የሱፐርቪዥን ቡድን አባላቱ ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

 

አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ÷ መንግስት የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ከዚህ አኳያ በክልሎች ከሪፖርትና ግምገማ ባሻገር የሱፐርቪዥንና ግብረ መልስ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

 

ይህም የመንግስት ኢኒሼቲቮችና ፖሊሲዎች አፈጻጸምን በተግባር ለማየት እንዲሁም ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋት እንደሚያግዝ ነው ያነሱት።

 

በተጨማሪም በክልሎች መካከል የአፈጻጸም ልዩነቶችን ለማጥበብ እንደሚያግዝ አንስተው፤ ይህም ለዜጎች ልማትን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸሃይ ጳውሎስ÷ የሱፐርቪዥን ስራዎቹ ችግሮችን ቀርቦ የማየትና የመረዳት፤ ህዝብን የመደገፍ እንዲሁም የተሻሉ ተሞክሮዎችን የማስፋት ዓላማ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

 

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል÷ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራዊ ምላሾችን ለመስጠት መሰል የሱፐርቪዥን ስራዎች ሚናቸው የጎላ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

 

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ፈቃዱ ተሰማ በበኩላቸው÷ የሱፐርቪዥን ስራው የአመራር አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡

 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)÷በመስክ ምልከታ ስራዎች በየአካባቢው የተለያዩ ምርጥ ተሞክሮዎች መገኘታቸውን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አመራሩ ህዝብ ጋር ተቀራርቦ በሚያከናውናቸው ስራዎች የኢትዮጵያን የልማት አቅሞች ጥቅም ላይ ለማዋል ያግዛል ያሉት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶች እና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ናቸው፡፡

 

አቶ አደም ፋራህ በሰጡት ማጠቃለያ÷ በመስክ ምልከታው የተለዩና በየደረጃው ባሉ የመንግስት መዋቅሮች ሊፈቱ የሚገቡ ችግሮችን ለይቶ መቅረፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

 

Exit mobile version