Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢራን አዲስ የፀረ አውሮፕላን ሚሳኤል ስርዓት ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኤሮስፔስ ቡድን የሀገሪቱን የኑክሌር መሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ አዲስ የፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤል ስርዓት ይፋ አድርጓል፡፡

በኢራን ታሪክ እጅግ ዘመናዊ የተባለው የፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤል ስርዓት በኢራን የኤሮስፔስ ቡድን የተገጣጠመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

358 የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የአየር መቃወሚያ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በዛሬው እለት ባደረገው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ልምምድ ላይ የተሳካ ሙከራ ማድረጉ ተገልጿል።

በኢራን ኢስፋሃን ግዛት በተደረገው የአየር ልምምድ አዲሱ የፀረ -አውሮፕላን ሚሳኤል ስርዓት 30 የአየር ላይ ኢላማዎችን ለማምከን የተሰጠውን ሙከራ ሁሉንም ኢላማዎች በመምታት የተሳካ ሙከራ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

የሚሳኤል ስርዓቱ ከማንኛውም ቦታ በኢራን የአየር ክልል የተተኮሰን ሚሳኤል መትቶ ማክሸፍ እንደሚችል ተነግሯል።

በተጨማሪም አውሮፕላን የተነሳበትን ቦታ በፍጥነት በመርመር እንቅስቃሴውን በመከታተል መምታት ይችላል ተብሏል፡፡

የአየር መቃወሚያው በዋናነት የሰው አልባ ድሮኖችን፣ ሄሊኮፕተሮችን፣ የጦር አውሮፕላኖችን እንዲሁም ሌሎች በአየር ላይ የሚሰነዘሩ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴዎችን ለማምከን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የወታደራዊ ልምምዱ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አሊ ሞሀመድ ናይኒ÷ ከ10 ቀናት በኋላ ከ300 በላይ የጦር መርከቦች የተሳተፉበት ሰፊ የባህር ሐይል ልምምድ በፋርስ ባህረ ሰላጤ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም አብዮታዊ ዘቡ አቅሙን ለማሳየት በመጭው አርብ 110 ሺህ ተዋጊዎችን ያሳተፈ የእግረኛ ጦር ልምምድ እንደሚደረግ ጠቁመው÷ ኢራን ለማንኛውም አይነት ጦርነት ዝግጁ ናት ማለታቸውን ዘ ታይም ኦፍ ኢንዲያ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version