አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት በዲጂታል አማራጮች የ5 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ዝውውር መፈፀሙን አስታወቀ።
የባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ ዲቪዥን መርቻንትና ኤጀንት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ብሌን ኃይለሚካኤል እንዳሉት÷ባንኩ 30 ሚሊየን የሲቢኢ ብርና 9 ሚሊየን የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች አሉት።
በተጨማሪም 21 ሚሊየን የካርድ ባንኪንግ እና 4 ሺህ በላይ የፖስ ማሽን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ነው የገለጹት፡፡
በእነዚህ የዲጂታል አማራጮችም ባለፉት ስድስት ወራት 910 ሚሊየን ግብይቶች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በዚህም የ5 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ዝውውር የተፈጸመ ሲሆን፥ አሁን ላይም 79 በመቶ የባንኩ የገንዘብ ዝውውር ሥራ በዲጂታል አማራጮች እንደሚካናወን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡