የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ ከ29 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

By Feven Bishaw

January 08, 2025

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ29 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው የቱሪዝም ልማት እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን ታደሰ÷የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት፣ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠርና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት 11 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲሁም ከ100 ሺህ በላይ የውጪ ቱሪስቶች በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

በዚህም 31 ቢሊየን ብር ከዘርፉ ለማግኘት ታቅዶ ከ29 ቢሊየን ብር በላይ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ቢሮው በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን ይበልጥ ለማዘመን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀው 76 ለሚሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች አስፈላጊው መሰረት ልማት መሟላቱን አስታውቀዋል፡፡

በኢኮ ቱሪዝም ዘርፍም የሚበረታቱ ስራዎች መሰራታቸውንም ነው አቶ ፋንታሁን የጠቆሙት፡፡

በጸሃይ ጉሉማ