Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በ84 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዳግም ምዝገባ እንዲያካሄዱ ጥሪ ቀርቦላቸው ምዝገባ ባላካሄዱ  84 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰዱን የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

 

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ማርታ አድማሱ÷ወጥነት ያለው የፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት እንዲተገበር የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳግም ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል ፡፡

 

በዳግም ምዝገባውም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የተሳሳተ ሰነድ ካላቸው እንዲያስተካክሉ አልያም የጎደለውን እንዲያሟሉ እድል ተሰጥቷቸው እንደነበርም ተናግረዋል ።

 

ዳግም ምዝገባ እንዲያደርጉ ጥሪ ከቀረበላቸው 102 ተቋማት ውስጥም 84 የሚሆኑት ዳግም ምዝገባ አለማድረጋቸውን ገልጸው ምዝገባ ያላከናወነ ተቋም በራሱ ፈቃድ ከመማር ማስተማር ስራው እንደወጣ ይቆጠራል ብለዋል ።

 

እነዚህ ተቋማትም ከመማር ማስተማር ስራው ሲወጡ የመውጫ ፎርም እንዲሞሉ የሁለት ሳምንት ጊዜ ገደብ እንደተሰጣቸውም  የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል ።

 

አሁን ላይ አምስት ተቋማት ብቻ ይህንን ሂደት የጀመሩ ሲሆን÷ ወደዚህ ስራ ያልገቡ ቀሪ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ በፍታብሄር እና በወንጀል ህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል ፡፡

 

ተቋማቱ ከዚህ በኋላ በሰነድ የታገዘ ምዝገባ እንደማያደርጉ እና ዳግም ወደ መማር ማስተማር ስራው እንደማይመለሱም አረጋግጠዋል፡፡

 

በቀጣይም ዘጠኝ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀው በተቋማቱ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎችን አስፈላጊውን መረጃ በማሟላት እስከ ጥር ወር 2017ዓ.ም መጀመሪያ ድረስ ፈቃድ ወዳላቸው ተቋማት እንዲያዛውሩ ትዕዛዝ መሰጠቱንም አብራርተዋል ፡፡

 

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version