Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ርዕሳነ መስተዳድሮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት (ገና) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ÷ኢትዮጵያ የብዝሃ እምነት፣ ባሕልና ቋንቋ መገኛ ድንቅ ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡

አንዱ የሌላውን እምነት፣ ባሕል፣ ታሪክና ቋንቋ አክብሮ እንደ ድርና ማግ ተዋህዶ በፍቅር የሚኖርባት ምድር ናት ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ታላቁን የገና በዓል ስናከብርም የታረዙትን በማልበስ፣ የተራቡትን በማጉረስ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና የታመሙትን በመጠየቅ የቀደመ የመረዳዳት ባሕላችን ሳንዘነጋ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ÷ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት አንዱ የሆነው የገና በዓል ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር የተገለፀበት ታላቅ መንፈሳዊ በዓል መሆኑን ገልፀዋል።

በዓሉን ስናከብርም በተለያየ አይነት ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን በማሰብ እና በተቻለን አቅም በፍቅር እና በልግስና ያለንን በማካፈል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የይቅርታ፣ የእርቅ እና ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሸጋገር ምልክት ነው ብለዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በዓሉ የፍቅር፣ የጤና፣ የሰላምና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version