የሀገር ውስጥ ዜና

የርዕደ መሬት ስጋት ላለባቸው ዜጎች 281 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

By yeshambel Mihert

January 04, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የርዕደ መሬት ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች እስካሁን ከ281 ሚሊየን 562 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፉ መደረጉን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በአፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰተ ባለው የርዕደ- መሬት ክስተት ሁኔታና ምላሽን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም÷በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ የርዕደ መሬት ክስተት የተፈጥሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ደወልን ተከትሎ መንግስት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በእስካሁኑ ሁኔታና ምላሽ እየታየ ያለው ስራ አመርቂ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ÷በአፋር ክልል ሁለት ወረዳዎች ማለትም አዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ (ዱለሳ) ወረዳዎች ለችግሩ ተጋላጭ ናቸው ብሏል፡፡

በሁለቱም ወረዳዎች በአዋሽ ፈንታሌ 6 ተጋላጭ ቀበሌዎች 15 ሺህ ነዋሪዎች ተጋላጭ መሆናቸውን እና እስከ አሁን 7 ሺህ ወገኖች ከስጋቱ ቀጣና ወደ ሌላ ስፍራ መጓጓዛቸውን ጠቁሟል፡፡

በዱለቻ ወረዳ ደግሞ 20 ሺህ የሚሆኑ በ2 ቀበሌዎች የሚገኙ ወገኖች ተጋላጭ ሲሆኑ÷ ከእነዚህ ቀበሌዎች እስካሁን 6 ሺህ 223 ነዋሪዎች አካባቢውን እንደለቀቁ ተመላክቷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ የ5 ቀበሌ ወገኖች ለአደጋው ተጋላጭ መሆናቸውን የጠቀሰው መግለጫው÷በ5ቱም ቀበሌዎች 16 ሺህ 182 ነዋሪዎች ተጋላጭ ናቸው ተብሏል፡፡

እስካሁን ድረስ 7 ሺህ 350 ነዋሪዎች ከተጋላጭ ስፍራው የወጡ ሲሆን ÷8 ሺህ 832 የሚሆኑት ቀሪዎቹ ሰዎች ደግሞ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ከስፍራው እንዲንቀሳቀሱ እየተሠራ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡

ኮሚሽኑ ክስተቱን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጣ የሳይንቲፊክ ኮሚቴ ያለውን ሁኔታ እየተከታተለ መሆኑን በመጠቆም÷መገለጽ ያለባቸውን ቅድመ ጥንቃቄዎች አስመልክቶ አስፈላጊው መረጃ ለሕዝብ በተከታታይ እንደሚቀርብ አመልክቷል፡፡

መረጃዎችንም ከኮሚሽኑ ማህበራዊ ትስስር ገጾች እና ከድህረ ገጽ መከታተል እንደሚቻል ነው የተገለጸው፡፡

የርዕደ መሬት ንዝረቱ ባለበት አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ከንዝረቱ በፊት፣ በንዝረቱ ወቅትና ከንዝረቱ በኋላ መውሰድ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች እንዲወስዱ አስፈላጊው መረጃ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡

ሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከተ እስከ አሁን ለ70 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን 11 ሺህ 550 ኩንታል ምግብ-ነክ እና ለ700 አባወራ የሚሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ስፍራው ተልኳል ነው የተባለው፡፡

ይህም በንዘብ ሲተመን ለምግብ ብር 216 ሚሊየን 562 ሺህ ብር በላይ እና ምግብ ነክ ላልሆኑ ቁሳቁሶች 65 ሚሊየን 625 ሺህ ብር በድምሩ 281 ሚሊየን 562 ሺህ ብር በላይ የሚገመት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የርዕደ መሬቱን ባህሪያትና የሚጠይቀው የጥንቃቄ መልዕክት በተከታታይ እንደሚያቀርብ የጠቀሰው የኮሚሽኑ መግለጫ÷በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ አደጋውን ለመሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረትና በንቃት እንዲንቀሳቀሱ አሳስቧል፡፡