አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለገና በዓል አስፈላጊ የፍጆታ እቃዎች በበቂ ሁኔታ ለገበያ መቅረባቸውን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ÷ በክልሉ ለገና በዓል የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ግብዓቶችን ለገበያ ለማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቂ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡
በሁሉም አካባቢዎች በተዋረድ ኮሚቴ ተዋቅሮ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ እቃዎች ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡
በዚህም 460 ሺህ ቶን በላይ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ስንዴ ዱቄት፣ በቆሎና ገብስን ጨምሮ ከ195 ሺህ ኩንታል በላይ እህል ለገበያ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም 336 ሺህ ፍየል፣ 277 ሺህ በግ፣ 9 ሚሊየን ዶሮ እና 30 ሚሊየን እንቁላል በ441 የእሑድ ገበያ ማዕከላት ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል በመንግስት ከሚቀርበው የምግብ ዘይት በተጨማሪ 10 ሚሊየን ሊትር ዘይት ለገበያ መቅረቡን ነው ም/ሃላፊው ያብራሩት፡፡
ለበዓሉ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ጥራትና ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ሕብረተሰቡ ከሃሰተኛ ገንዘብ፣ ባዕድ ነገር ከተቀላቀለባቸው እና የመጠቀሚያ ጊዜ ካለፈባቸው ምርቶች እንዲጠነቀቅ አስገንዝበዋል፡፡
ሸማቹ ማህበረሰብ በግብይት ወቅት አጠራጣሪ ነገሮች ሲመለከት አቅራቢያ ለሚገኙ ጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በመላኩ ገድፍ