አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረገው ምክክር ጠቃሚ ግብአቶችን ማሰባሰብ መቻሉ ተገለጸ።
ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ባሉ እና በቀጣይ ሊያከናውናቸው ባቀዳቸው ጉዳዮች ላይ ከኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) እና ኮሚሽነሮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ተግባራት፣ ባጋጠሙ ተግዳሮቶች እና በቀጣይም ኮሚሽኑ በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር በአካል በመገናኘት ያላቸውን አጀንዳ እና ጥያቄ በማዳመጥ ለማሰባሰብ ከሚሲዮኖች በሚፈልጋቸው ትብብሮች ላይ ገለጻ ቀርቧል።
ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን እና የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያለው ሚና ላይም ገለጻ መደረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አካታች፣ ነጻ እና ገለልተኛ በመሆን በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም የዳስፖራ አደረጃጀቶች ጋር ምክክር ሲያደረግ መቆየቱ ተገልጿል።
በዚህም ጠቃሚ ግብአቶችን ማሰባሰብ መቻሉ ተጠቅሷል።