አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያደረገችውን ስምምነት መሠረት በማድረግ ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በሣምንታዊ መግለጫው የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ፣ ጂኦፖለቲካና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ከሶማሊያ ጋር የተፈረመውን ስምምነት መሠረት በማድረግ በሁለቱ ሀገራት መካከል ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶች እየተደረጉ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል።
ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እና የጋራ ጠላታቸው የሆነውን አል-ሻባብን ለመዋጋት ቀጣናውን ከሽብርተኝነት ለማፅዳት ከስምምነት መድረሳቸውንም አንስተዋል።
በሶማሊያ በድህረ-አትሚስ የሚኖረው የኃይል ስምሪትን በተመለከተም ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚኖራት ሚና ለቀጣናውም ሆነ ለዓለም ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ታምናለች ብለዋል።
የሀገራቱ ውይይት ቀጥሎ በቅርቡ በአዲስ አበባ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም በተለይም በሱዳን ያለው ግጭት ወደ ሰላም እንዲመጣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የምታደርገውን ጥረት ትቀጥላለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የሱዳን ቀውስ እንዲቆም የምታደርገው ጥረት ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም የምታደርገው ጥረት ማሳያ ነውም ብሏል ሚኒስቴሩ።
በውብርስት ተሰማ