ፋና ስብስብ

በአንበሶች ግዛት ለቀናት ፍራፍሬ እየተመገበ የቆየው ታዳጊ…

By Meseret Awoke

January 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቲኖቴንዳ የተባለው የ8 ዓመት ታዳጊ በአናብስት ግዛት ለቀናት ያለምንም ጭረት መቆየት መቻሉ በርካቶችን አስገርሟል፡፡

በሰሜናዊ ዚምባብዌ የሚገኘው ማቱሳዶና አናብስቱ ሲያገሱ፤ ዝሆኖች በግዙፍ አካላቸው ሲርመሰመሱ የሚታይበት አስፈሪ ግዛት ነው፡፡

በዚህ ግዛት የሰው ልጅ ለመጎብኘት ሲገባ እንኳን በጠባቂዎች ታጅቦና ደህንነቱ አስጊ አለመሆኑን አረጋግጦ ቢሆንም የፍርሃትን መቀነት ታጥቆ ነው፡፡

በአካባቢው ከሰሞኑ የተሰማው ግን በርካቶችን አስገርሟል፡፡ የሥምንት ዓመቱ ታዳጊ በግዛቱ ከአንበሶች መንጋጋ፤ በዝሆኖች ግዙፍ አካል ለጥቃት ከመዳረግ ተርፏል፡፡

ታዳጊው ለሰዓታት ወይም ለአንድ ለሁለት ቀናት ሳይሆን ለአምስት ቀናት በአራዊቱ ግዛት ቆይቶ በሕይወት ወጥቷል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡

ክስተቱ የጀመረው ቲኖቴንዳ ፑዱ ከቤቱ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና አስፈሪ በሆነው የማቱሳዶና ፓርክ አካባቢ ሲጓዝ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ታዳጊው ትራሱን ድንጋይ፤ ጣራውን ሰማይ አድርጎ በሚያገሱ አናብስት መካከል የዝሆኖችን ልፊያ በሚፈጥረው አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ለአምስት ቀናት የዱር ፍራፍሬዎችን ከእንስሳት እኩል እየተመገበ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

የማቱሳዶና ፓርክ 40 አናብስት ያሉት ሲሆን ፥በአንድ ወቅት በአፍሪካ ከፍተኛ የአንበሳ ቁጥር ያለበት ፓርክ እንደነበር የአፍሪካ ፓርኮች መረጃ ያመላክታል፡፡

ታዳጊው ስለዱር እና ራስን ስለማዳን ያለውን እውቀት አሟጦ በሕይወት ለመቆየት ተጠቅሞበታል ሲልም የሀገሪቱ ፓርኮችና የዱር እንስሳት አስተዳደር ባለስልጣን ገልጿል።

የአካባቢው የኒያሚንያሚ ማህበረሰብ አባላት ታዳጊውን ለማግኘት በየቀኑ ከበሮ በመምታት ድምጽ ለማሰማት ሲሞክሩ ቢቆዩም ፥ በመጨረሻ ግን ታዳጊውን ያገኙት የፓርኩ ጠባቂዎች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡

ፓርኩ ከ1 ሺህ 470 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ያለው ሲሆን ፥ የሜዳ አህያ፣ ዝሆኖች፣ ጉማሬዎች፣ አንበሶች እና የሌሎች እንስሳት መኖሪያ ነው።