Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዩኒቨርሲቲ አመራሮች በአካባቢያዊነት የሚመደቡበትን ሥርዓት ለማቆም እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት÷ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይም የዩኒቨርሲቲ አመራሮች በአካባቢያዊና በመንደር የሚመደቡበት ሥርዓት መቆም አለበት በሚል በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የዓለም አቀፍ እውቀት መማሪያና የማስተማሪያ ተቋማት እንጂ የአንድ አካባቢን ሰዎች ተቀብለው የሚያስተናግዱ አይደሉም ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡

አሰራሩ ከዩኒቨርሲቲ መሰረታዊ ተልዕኮ ጋር እንደማይሄድ ጠቁመው÷አዲስ የሚመደቡና የሚቀየሩ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እንደ መርሕ በችሎታና በውድድር ብቻ የመመደብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲን ካለበት መሰረታዊ ችግር ለማላቀቅ የአመራር ለውጥ ከተደረገ በኋላ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች እውቀትና እውነት የሚገበይባቸው ትክክለኛ የማስተማሪያና የምርምር ተቋማት ሊሆኑ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ድሪባ ኢቲቻ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ አዲስ አመራር ከተመደበ በኋላ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች እንደተከናወኑ መናገራቸውን የሚስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version