አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግስት ቤቶችና መሬት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ግል ይዞታ እንዳይዛወር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ፍትሕ ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋየ ደጀኔ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በመዲናዋ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን እና ሕገ- ወጥ ተግባራትን ለማረም እየተሰራ ነው።
በተለይም የመሬት ወረራና በሕገ-ወጥ መንገድ የመንግስትን መሬትና ቤቶች በሚይዙ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
ባለፉት አምስት ወራት ኦዲትና ኢንስፔክሽን በማድረግ በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዘ መሬትና ቤቶችን የማስመለስና በወንጀል ተጠያቂ የማድረግ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም በሕገ ወጥ መንገድ ለግል አላማ ሊውል የነበረን 109 ሔክታር መሬት በፍ/ቤት ክርክር ማስመለስ መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡
ከቀበሌ ቤቶች ጋር ተያይዞ የቤቶችን ሰነድ ማጥፋት፣ ቤቶችን ከሌላ ይዞታ ጋር መቀላቀል እና በፍ/ቤት ውሳኔ በሚል ወደ ግል ማዞር በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
የቀበሌ ቤቶች በአዋጅ 47/67 የተወረሱና በመንግስት የሚተዳደሩመሆኑን ገልጸው÷ባለፉት ዓመታት ቤቶቹን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ግል የማዛወር ሒደት እንደነበር አብራርተዋል፡፡
አሁን ላይም ውስን የሆነውን የመንግስት ሃብት ወደ ግል ለማዞር የሚደረገውን ሒደት በማክሸፍ ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አራት ወራትም ኮንዶሚኒየሞችን ጨምር ከ84 በላይ የሚሆኑ የመንግስት ቤቶችን በፍርድ ቤት ክርክር ማስመለስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ከሕግ አግባብ ውጪ ተይዘው የነበሩ 23 ሼዶችን በፍርድ ቤት ውሳኔ በማስለቀቅ ለወጣቶች በሥራ እድል ፈጠራ እንዲተላለፍ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ