አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥራ በሆነው የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ በአሶሳ ከተማ እየተገነባ ያለው ሙዝዬም እና ቤተ-መጻሕፍት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አድማሱ ተክሌ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ከመጽሐፍ ሽያጩ ገቢ ባለሦስት ወለል ሙዝዬም እና ቤተ-መጻሕፍት እየተገነባ ነው፡፡
ሙዝዬም እና ቤተ-መጻሕፍቱ በውስጡ የስብሰባ አዳራሾች፣ ባሕላዊ የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች፣ ለጥናትና ምርምር የሚያገለግሉ የአይሲቲ ክፍሎች እና አንፊ ቴአትሮች ያሉት መሆኑን ገልጸዋል።
መጀመሪያ ለመገንባት ታስቦ የነበረው ባለሁለት ወለል መሆኑን እና በወቅቱም 247 ሚሊየን 274 ሺህ ብር በጀት ተይዞለት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በኋላ ላይ በተደረጉ ምክክሮች ግንባታው ባለሦስት ወለል እንዲሆን መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸው÷ ከዚህ ጋር ተያይዞ መጀመሪያ የተያዘው የገንዘብ መጠን እና የጊዜ ገደብ ሊጨምር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
አጠቃላይ የግንባታው አፈጻጸም 51 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው÷ በተያዘው ዕቅድ መሰረት እስከ ሕዳር ወር 2018 ዓ.ም ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው