የሀገር ውስጥ ዜና

ሚዲያዎች ገዢ ትርክትን ለመፍጠር በትኩረት ሊሰሩ ይገባል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

By Melaku Gedif

December 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ የገነባውን ዘመናዊ ስቱዲዮ ጎብኝተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት÷አሚኮ የገነባቸው የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስቱዲዮዎች መንግስት ለጠንካራ ሚዲያ ግንባታ የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡

ሚዲያ ለኅብረተሰብ ለውጥ በመትጋት፣ የመንግሥትን ሥራዎች ለሕዝብ በማድረስና ገዥ ትርክት በመፍጠር ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና አንደሚጫወት አውስተዋል፡፡

አሁን ያለንበት ዘመን እያንዳንዱ ግለሰብ በያዘው ዲጂታል መሣሪያ፣ መረጃ ያለ ገደብ የሚያሠራጭበት ነው ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ይህንን ታሳቢ ያደረገ የይዘት ጥራት፣ ፍጥነትና ተደራሽነት ላይ በስፋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

እንደ ሀገር የተጀመረውን ሁለንተናዊ ሪፎርም በትጋት፣ ፍጥነትና ጥራት ለመፈፀም ሚዲያዎች ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡