የሀገር ውስጥ ዜና

የኢንዱስትሪ ዘርፍ ስራ እድል የመፍጠር አቅም ከ156 ሺህ በላይ መድረሱ ተገለጸ

By amele Demisew

December 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ ዓመታት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ዓመታዊ የስራ እድል የመፍጠር አማካኝ አቅም ከ156 ሺህ በላይ መድረሱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደገለጹት÷ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኤክስፖርት ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውስጥ ገበያ ማምረት እንዲችሉ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ተወዳዳሪነታቸው እንዲያድግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አንስተዋል።

በዚህም በአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ላይ ማሻሻያ በመደረጉ፤ ከለውጡ በፊት ወደ 46 በመቶ ወርዶ የነበረው የማምረት አቅም አሁን ላይ ወደ 60 በመቶ ማደግ መቻሉን ጠቁመዋል።

ከለውጡ በፊት 30 በመቶ የነበረው የዘርፉ የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ አሁን ላይ ወደ 40 በመቶ ማድረስ መቻሉንም ገልጸዋል።

በለውጡ ዓመታት በዘርፉ ዓመታዊ የስራ እድል የመፍጠር አማካኝ አቅም ከ156 ሺህ በላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪው የውጭ ባለሀብቶች ፍሰትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ወደ ማምረት የሚገቡ የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።