የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ለበዓሉ የግብዓት አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር እየተሰራ ነው

By Mikias Ayele

December 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ለገና በዓል ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋና በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በመዲናዋ የተቋቋመው የገበያ ማረጋጋትና ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ሃይል ለገና በዓል ገብያን ለማረጋጋት እያከናወናቸው የሚገኙ ተግበራት ተገምግመዋል፡፡

በመድረኩ የግብይት ቦታዎችን በማመቻቸትና የምርት አቅርቦትን በመጨመር የበዓል ግብዓቶች ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕግን በማስከበር፣ የገቢ አሰባሰብ በመጨመርና የእሑድ ገበያን በማስፋት ረገድ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውና ውጤት ማምጣታቸውም ተመላክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባና የግብረ ሃይሉ ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ÷ መጪውን የገና በዓል ህብረተሰቡ በተረጋጋ መልኩ እንዲያከብር ግብረ ሃይሉ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

የባዛር ቦታዎችን ምቹ በማድረግ፣ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር በቅንጅት በመስራት እንዲሁም ስራዎችን  በየጊዜው በመገምገም ለሚያጋጥሙ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባም አስግንዝበዋል፡፡

የከተማ አስተዳሩ የንግድ ቢሮ ሃላፊ  ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ  በበኩላቸው ÷ ለመጪው  በዓል  የግብዓት አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአቅርቦትና የዋጋ ጭማሪ  እንዳይፈጠር የሚደረገውን ክትትልና ቁጥጥር በማጠናከር የበዓል ምርቶች በተገቢው መልኩ ለነዋሪዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ይሰራል ማለታቸውንም የአስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡