የሀገር ውስጥ ዜና

ብልፅግና ፓርቲ ሰው ተኮር መሆኑን አሳይቷል – ከንቲባ ከድር ጁሃር

By ዮሐንስ ደርበው

December 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልፅግና ፓርቲ በከተሞች አገልግሎትን በማሻሻልና አካታችነትን በማረጋገጥ ሰው ተኮር መሆኑን አሳይቷል ሲሉ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

ፓርቲው ያስቀመጠው አቅጣጫ በትክክለኛ አፈጻጸም እየተተገበረ ነው ያሉት ከንቲባው÷ በድሬዳዋ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከመልካም አስተዳደርና ከሪፎርም ስራዎች አንፃር በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

በአስተዳደሩ ህብረተሰቡ ባለበት ቦታ ሆኖ በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል የዲጂታል መሰረተ ልማት በ32 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በመጠናቀቅ ላይ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በከተማዋ የሚገኙ ከ400 በላይ ተቋማት ለደንበኞቻቸው ዲጂታል አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

በፓርቲው አቅጣጫ መሰረት በከተሞች አካታች ልማትና አገልግሎትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ያላቸው በተለይም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩና አቅመ ደካሞችን የሚደግፉ ኢኒሼቲቮች መተግበራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም የምገባ አገልግሎት፣ የዳቦ ፋብሪካዎች እና የአቅመ ደካሞች የቤት ዕድሳት የፓርቲውን ሰው ተኮር እሳቤ በተግባር የገለጡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደርም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተተገበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ አገልግሎት እየተሻሻሉ ናቸው ብለዋል።

ሪፎርሙ በከተሞች በህዝቡ ቅሬታ ሲነሳባቸው የነበሩ ወሳኝ የሚባሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከፍተኛ ለውጥ እንዲያሳዩ አድርጓል ነው ያሉት።

በቀጣይም የከተሞችን አገልግሎትና መልካም አስተዳደር ይበልጥ ለማሻሻል የዲጂታል መታወቂያና መሰል ምቹ ምህዳሮች በተጠናከረ መልኩ እንደሚተገበሩ አመላክተዋል፡፡