Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኤር ካናዳ አውሮፕላን ለማረፍ ሲሞክር በእሳት መያያዙ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ንብረትነቱ የኤር ካናዳ የሆነ አውሮፕላን የቴክኒክ ችግር አጋጥሞት ለማረፍ ሲሞክር በእሳት ተያይዞ እንደነበር ተገለጸ።

የበረራ ቁጥር 2259 የሆነ ይህ አውሮፕላን ትናንት ማታ በሃሊፋክስ ስታንፊልድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲሞክር አንደኛው ጎማ አልዘረጋ ብሎት ተንሸራቶ መስመር በመሳቱ በእሳት መያያዙ ተነግሯል።

ደጋው በሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ያላደረሰ ሲሆን 73 መንገደኞችና የበረራ ሰራተኞች በፍጥነት ከአውሮፕላኑ እንዲወጡ መደረጉ ነው የተገለጸው።

አንድ መንገደኛ፤ አውሮፕላኑ ለማረፍ ሲሞክር አንዱ ጎማ አልዘረጋ እንዳለውና መሬት ሲነካ የፍንዳታ ድምፅ እንደሰማች ለሲቢሲ ተናግራለች።

አውሮፕላኑ ለማረፍ ሲሞክር ከመንደርደሪያው ተንሸራቶ መውጣቱንና ክንፍ እና ሞተሩ ከመሬቱ ጋር ሲጋጩ የፍንዳታ ዓይነት ድምፅ መሰማቱን አናዶሉ ዘግቧል።

አደጋውን ተከትሎ አውሮፕላን ማረፊያው ለጥንቃቄ በሚል ለሰዓታት ከተዘጋ በኋላ መልሶ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ዘገባው ጨምሮ ጠቅሷል።

የአደጋውን መንስኤ የሀገሪቱ የአቪየሽን ባለስልጣናት እየመረመሩ ስለመሆኑ በዘገባው ተመላክቷል።

Exit mobile version