የሀገር ውስጥ ዜና

 ብልፅግና ቃልን በተግባር እየፈጸመ ያለ ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ነው – ርዕሳነ መስተዳድሮቹ

By Mikias Ayele

December 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልፅግና ቃልን በተግባር እየፈጸመ ያለ ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ መሆኑን ደቡብ ኢትዮጵያና ሲዳማ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለፁ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት÷ በኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩና የሚነጣጥሉ ትርክቶችን ስብራት ለመጠገን ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

እንደ ሀገር የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ችግር ለህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ማጣት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህ ረገድ ፓርቲው መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የቆዩ ስብራቶችን በመጠገን አሰባሳቢና ገዥ ትርክቶችን በመፍጠር አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

ፓርቲው ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በዚህም ለዓመታት እየተንከባለሉ የመጡ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ የክልልነት ጥያቄ ምላሽ የተሰጠበት አግባብ በትልቅ ማሳያነት እንደሚወሰድም ገልጸዋል፡፡

በኢኮኖሚ ዘርፍም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ የስንዴ ልማት፣ የመስኖ ስራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የቱሪዝም ማስፋፊያ፣ በኮሪደር ልማትና የህዳሴ ግድብ ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

መርሐ-ግብሩ በክልሉ በገጠርና በከተማ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማርባት ለቤተሰብ ፍጆታ ከመጠቀም ባለፈ ለበርካታ ሰዎች የገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት ስራው ለማሕበረሰቡ በርካታ የስራ እድል መፍጠር ማስቻሉን ገልጸው፤ በምግብ እራስን ለመቻልም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሲዳማ ክልል የሌማት ትሩፋት ስራ ባሕል እየሆነ መምጣቱን የገለፁት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ ከእለት ወደ እለት የማሕበረሰቡ ተጠቃሚነትም እንዲሰፋ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የሌማት ትሩፋት ስራ የበለጠ ለውጥ እንዲያመጣ የእያንዳንዱን ነዋሪ ተጠቃሚነት የመፈተሽ ስራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡