የሀገር ውስጥ ዜና

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ ተጨባጭ ስኬት አምጥቷል – ማሞ ምህረቱ

By Melaku Gedif

December 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥና ተጨባጭ ስኬት ማምጣቱን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከተከናወኑ ትላልቅ የሪፎርም ስራዎች መካከል በተለይም በኢኮኖሚ ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት ማሞ ምህረቱ፤ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ታሪካዊና በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው የዋጋ ንረትን መቋቋም በሚያስችል መልኩ የተከናወነና ውጤቱም የተሳካ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።

ከገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው በፊት የምርትና ምርታማነት እጥረት እንዲሁም የዋጋ ንረት ሀገሪቱን ሲፈትናት እንደነበር አስታውሰው፤ ከማሻሻያው በኋላ ግን የዋጋ ንረቱ ከነበረበት 30 በመቶ አሁን ላይ ወደ 16 በመቶ ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ የተደረገው ማሻሻያ በኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰው በቀጣይም የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነትን በሚፈለገው ልክ ለማስተካከል የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያን በየጊዜው ሲፈትናት የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሰረታዊ በሚባል መልኩ ያቃለለ ከመሆኑም ባለፈ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ክምችቱ ከ200 ፐርሰንት በላይ ከፍ እንዲል ማድረጉን ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ መስፋት ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ምርታማነትን በማሳደግና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

ከዓመት ዓመት እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማነቱን አስጠብቆ ለማስቀጠል የተለያዩ ማሻሻያዎች የተደረጉ ሲሆን የፋይናንስ ዘርፉ በሚሰበስበው ቁጠባና በሚያበድረው ብድር በየዓመቱ ከ25 በመቶ በላይ ዕድገት የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የታክስ አሰባሰቡ እያደገ መምጣቱንና የመንግስት የውጭ ዕዳዎች እየተቃለሉ መምጣታቸውንም ነው ያብራሩት።

የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎቹ የተቀናጁና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርጉ በመሆናቸው በተለይም የኤክስፖርት ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ እያበረታቱ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።