የሀገር ውስጥ ዜና

የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል ገቡ

By Mikias Ayele

December 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የሰላም አማራጭን በመከተል የትጥቅ ትግልን በመተው የህዝብንና የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች ወደ ተዘጋጀላቸው የተሃድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል ገቡ።

ታጣቂዎቹ በተሳሳተ መንገድ ወደ ትጥቅ ትግል ገብተው ህዝብ ላይ ያደረሱትን በደል ለማካካስ እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመዋል።

በክልሉ የሰላም መደፍረሱ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን በመቀበል መግባት መጀመራቸው ተገልጿል።

በዛሬው እለትም በዋግኽምራ ብሔረሰብ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ከሰሜን ሸዋ ዞኖች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ተሀድሶ ማሰልጠኛው ማዕከል መግባታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን አመልክቷል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ቢኖሩም ለማስመለስ የሄድንበት መንገድ የተሳሳተ ነው ያሉት ታጣቂዎች፤ የሕዝብ ጥያቄ እናስመልሳለን ብለን ጫካ ከገባን በኃላ የፈጸምነውን ድርጊት የተሳሳተ በመሆኑ ሕዝቡ ላይ የከፋ በደል አድርሰናል ብለዋል።

በዚህም መጸጸታቸውን ገልጸው፤ የበደልነውን ህዝብ ለመካስ መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ሲሉ ገልጸዋል።

ሌሎች ጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችም የተሰለፉበት ዓላማ የተሳሳተና ሀገርና ሕዝቡን የሚጎዳ መሆኑን ተገንዝበው የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ መክረዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምስራቅ እዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ምክትል አዛዠ ኮሎኔል ወንድየ መንገሻ በበኩላቸው፤ የሰላም እጦት ሕዝብን እና ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን በመገንዘብ ጫካ ያሉ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ እንዲከተሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የሰላምን ጥሪ ተቀብለው ለሚመጡት የታጣቂ ቡድኑ አባላት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች እና ሌሎች እንግዶች መልካም አቀባበል እንዳደረጉላቸው ተገልጿል።