የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በትብብር እንደሚሰሩ ገለፁ

By Mikias Ayele

December 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ጅቡቲ በቀጠናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በትብብር እንደሚሰሩ ገለፁ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ ከጅቡቲ አቻው ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በዚህ ወቅት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያና ጅቡቲ የረጅም ዘመን ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ግንኙነታቸው በቀጠናው የመልካም ግንኙነት ምሳሌ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገች መሆኑን ገልጸው÷ በቀጠናው የሽብር እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘውን አል-ሻባብን ለመዋጋት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃሙድ አሊ የሱፍ በበኩላቸው÷ በሀገራቱ መካከል ያለው ወዳጅነት በህዝቦች ቤተሰባዊነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመጠቆም፣ ይህም ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም ለማስፈን  እያደረገች ላለው ጥረት አመስግነው÷ ኢትዮጵያ በቀጠናው አል-ሻባብን ለመዋጋት በምታደርገው ጥረት ጅቡቲ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡

በተጨማሪም  በውይይቱ የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በኢኮኖሚ፣ በንግድ እና በወደብ አገልግሎቶች ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ምክክር ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡