አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል አዳዲስ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እንዲስፋፉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠየቀ።
ቋሚ ኮሚቴው በትግራይ ክልል የሚገኙ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቋማት ላይ የመስክ ምልከታ እያደረገ ነው፡፡
የአራተኛ ትውልድ (4ጂ) ኔትወርክ፣ የዲጂታል ፋይናንሲንግ ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በክልሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ኮሚቴው አሳስቧል።
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ማህበረሰቡን የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስቧል።
በዚህም አገልግሎት ተቋርጦባቸው የነበሩ 498 ሰይቶች ወደ አገልግሎት መመለሳቸው የተገለጸ ሲሆን በሪጅኑ ከ320 ሺህ በላይ አዳዲስ ሲም ካርድ ተጠቃሚዎች፣ 32 ሺህ የቴሌብርና ከ57 ሺህ በላይ የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባና አገልግሎት በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በክልሉ ካሉ 93 ወረዳዎች ውስጥ በ27 ወረዳዎች የአራተኛ ትውልድ (4ጂ) ኔትወርክ ተደራሽ ሆኗል ተብሏል።
ኮሚቴው፣ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን የቴሌኮም አገልግሎትን ወደ ነበረበት ለመመለስ የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው ማለቱን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።