አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወባ በሽታን ለመከለከል እና ለመቆጣጠር በተሠራው ሥራ ሥርጭቱ እየቀነሰ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ኃላፊ እንዳሻው ሽብሩ ለፋና ዲጂታል ጋር እንዳሉት ባለፈው ዓመት ክረምት ወራት የወባ በሽታ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ እንደነበር እና በወቅቱ በሳምንት እስከ 40 ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች በወባ በሽታ ይያዙ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በተሠራው ከፍተኛ ርብርብ የበሽታው ሥርጭት መቀነሱን ነው ያስረዱት፡፡
የወባ መራቢያ ቦታዎችን የማፋሰስ እና የማዳፈን ስራ እንዲሁም ህብረተሰቡ አጎበርን በተገቢው መንገድ እንዲጠቀም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
በወባ በሽታ የተያዙ ሰዎች መድኃኒት እንዲያገኙ በአቅርቦት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱንም ገልፀዋል።
በዚህም በክልሉ በሳምንት በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 27 ሺህ ዝቅ ማለቱን የጠቆሙት ኃላፊው የወባ በሽታን የመከላከል ጉዳይ የሁሉም አካላት ቅንጅት የሚፈልግ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ ከፍተኛ ስርጭት የተስተዋለባቸው 21 ወረዳዎችን በመለየት ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው የወባ ሥርጭት ከፍተኛ ቁጥር ከተመዘገበባቸው አካባቢዎች በወላይታ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተሞች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ፀጋዬ ኤካ በበኩላቸውን የጤና ባለሙያዎች በስራ ሰዓት እና ከስራ ሰዓት ውጪ ጤና አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ እና የመከላከል ሥራ በንቅናቄ መልክ በመሠራቱ የወባ በሽታ ሥርጭት ቀንሷል ነው ያሉት።
በዞኑ በሳምንት የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 25 ሺህ ደርሶ እንደነበር ገልጸው በአሁኑ ወቅት ወደ 10 ሺህ መውረዱን ተናግረዋል።
በሁሉም ወረዳዎች እና ቀበሌዎች የቤት ለቤት ቅኝት እና አሰሳ መደረጉን ገልጸው የወባ ምልክት የሚታይባቸውን ሰዎች በመለየት ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በክልሉ የወባ በሽታ ሥርጭትን ሙሉ በሙሉ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከህብረተሰቡ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት ተከታታይ ሥራ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።
በዮናስ ጌትነት