አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላም ሚኒስትር ሙሐመድ እድሪስ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮችና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼኽ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ÷ የሙስሊሙን አንድነትና የሀገራችንን ሰላም ለማጠናከር ጠቅላይ ምክር ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንና ይህንም እንደሚያስቀጥል ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ በቀጣይ በሚያካሄደው የመጅሊስ ምርጫም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ በበኩላቸው በሰላም ግንባታና በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ጋር ያላቸውን ተቋማዊ ትብብር እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል፡፡
በአፋር እና በሶማሌ ወንድም ሕዝቦች መካከል የነበረውን አለመግባባትና ግጭት ለመፍታት ጠቅላይ ምክር ቤቱ ላበረከተው በጎ አስተዋጽኦም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም ሁሉንአቀፍ የሰላምና የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስቴሩ ከሁሉም የእምነት አባቶችና ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሠራ ገልፀው÷ መጭው የመጅሊስ ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲካሄድ መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡