ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ የሁቲ አማጺያን የሚሳዔል ማዕከል ላይ ጥቃት ፈጸመች

By Mikias Ayele

December 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በየመን በሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማጺያን የሚሳዔል ማከማቻ፣ ማዘዣ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተነግሯል።

የጥቃቱ ዓላማ አማጺያኑ በቀይ ባህር የመርከብ እንቅስቃሴ ላይ እያደረሱ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ መሆኑ ተገልጿል።

የአሜሪካ ጦር ሃይል እንዳስታወቀው፤ የተፈጸመው ጥቃት በአማጺያኑ የጦር መሳሪያ አቅም ላይ ጉዳት አድርሷል።

የጥቃቱ ዒላማ የነበረው በየመን ሰንአ የሚገኘው የሚሳዔል ማከማቻ፣ ማዘዣና መቆጣጠሪያ ማዕከል እንደሆነ ሬውተርስ በዘገባው አመልክቷል።

ማዕከሉ በኢራን ድጋፍ ይደረግለታል ተብሎ እንደሚታመንም ተጠቅሷል።

የአሜሪካ ጦር ሃይል ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ የተፈጸመው አማጺ ቡድኑ በደቡባዊ ቀይ ባህር፣ ባብ ኤል-ማንደብ እና በኤደን ባህረሰላጤ በአሜሪካ ባህር ሃይል የጦር መርከቦች እና በሌሎች የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ መሆኑን ገልጿል።