Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በ2024 ከሪሚታንስ ከፍተኛ ገቢ ያገኘች ቀዳሚ ሀገር – ሕንድ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፈረንጆቹ 2024 በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው በሚልኩት ገንዘብ (ሪሚታንስ) ሕንድ 129 ቢሊየን ዶላር በማግኘት ቀዳሚ መሆኗን ዓለም ባንክ አስታወቀ፡፡

በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎቿ ከፍተኛ ገቢ በማግኘት የምትታወቀው ሕንድ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 125 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷ ይታወሳል፡፡

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው በሚልኩት ገንዘብ የሚገኘው ገቢ ለሀገራት ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሲሆን÷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ነው።

በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆቹ ዓመት በዓለም የሪሚታንስ መጠን 685 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል።

ሕንድ ዘንድሮ ከሪሚታንስ ያገኘችው ገንዘብም የፓኪስታን እና ባንግላዲሽን ዓመታዊ በጀት ድምር የሚጠጋ መሆኑን ዓለምባንክ የገለጸው፡፡

ሜክሲኮ እና ቻይናም በ68 እና 48 ቢሊየን ዶላር ሕንድን ተከትለው በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎቻቸው ከፍተኛ ገቢ አግኝተዋል ተብሏል፡፡

በየዓመቱ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሕንዳውያን በትምህርት፣ በሥራ እና በሌሎች ምክንያቶች ከሀገር እንደሚወጡም ነው የተገለጸው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው 18 ሚሊየን ሕንዳውያን በተለያዩ ሀገራት ይኖራሉ፤ ወደ ሀገራቸውም ገንዘብ ይልካሉ።

የሕንድ ሪሚታንስ በአብዛኛው ከምዕራብ እስያ፣ ከሰሜን አሜሪካ እና ከአውሮፓ÷ በጤና፣ በቴክኖሎጂ እና በኮንስትራክሽን ዘርፎች ከተሰማሩ ባለሙያዎች የሚገኝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሲሆን÷ ባለፈው ዓመት በሪሚታንስ ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታውቋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው የሚልኩት ገንዘብ በሀገራቸው ልማት በንቃት እንዲሳተፉና የልማቱ ባለቤት እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

ዳያስፖራው ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ዋነኛ ተዋናይ እንደመሆኑ መጠን÷ በቀጣይ በሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡

Exit mobile version