ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ የአይኤስ መሪን ገደልኩ አለች

By Melaku Gedif

December 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ኃይል (ሴንትኮም) የአይኤሱን መሪ አቡ ዩሲፍን በአየር ጥቃት መግደሉን አስታውቋል።

አሜሪካ አቡ ዩሲፍን በባሽር አላሳድና በሩሲያ ኃይሎች ተይዞ በነበረ የሶሪያ ግዛት ውስጥ ባካሄደቸው የአየር ጥቃት መግደሏን ነው የገለጸችው።

የማዕከላዊ ዕዙ መሪ ማይክል ኤሪክ ኩሪላ አይኤስ የሶሪያን ወቅታዊ ሁኔታን እንዲጠቀምበት ዕድል አንሰጠውም ብለዋል።

አይኤስ በሶሪያ በእስር ላይ ያሉ ከ8 ሺህ በላይ አባሎቹን ለማስለቀቅ ዕቅድ እንደነበረው ገልጸዋል።

በሶሪያ ውስጥም ይሁን ከሶሪያ ውጭ በሚንቀሳቀሱ የአይኤስ አመራሮች ላይ ጥቃት መሰንዘራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት የዕዙ መሪ፤ ለዚህም ከአጋሮቻችን ጋር በትብብር እንሰራለን ማለታቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል።

በፈረንጆቹ 2014 አይኤስ በኢራቅና በሶሪያ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ጦርነት ተጠቅሞ የሀገራቱን ግዛቶች ተቆጣጥሮ እንደነበርና 12 ሚሊየን የሚሆኑ የሀገራቱ ዜጎች በስሩ ይተዳደሩ እንደነበር በመረጃው ተገልጿል።

በፈረንጆቹ ከ2019 ወዲህ በእነዚህ ሀገራት የነበሩትን አብዛኛዎቹን ይዞታዎች በጥምር ኃይሉ ጥቃት በማጣቱ በአሁኑ ወቅት ቡድኑ በሶሪያ፣ ኢራቅና አፍጋኒስታን ውስጥ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተመላክቷል።