የሀገር ውስጥ ዜና

የቢሾፍቱ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተማዋን ዘመናዊነት የሚያሻሽሉ ናቸው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

By Feven Bishaw

December 20, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢሾፍቱ የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተማዋን ገፅታ፣ ዘመናዊነትና የነዋሪዎቿን ኑሮ የሚያሻሽሉ ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ተስስር ገፃቸው፤ የሰባት ሐይቆች መገኛዋ ቢሾፍቱ በተቀናጀ የኮሪደር ልማት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በከተማዋ የተጀመሩ የተፈጥሮ ጸጋን ወደ ጥቅም የሚቀይሩ የልማትና የስማርት ሲቲ ተግባራት የሚበረታቱ እንዲሁም የቢሾፍቱን የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስት መናገሻነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ የከተማዋን ገፅታ፣ ዘመናዊነትና የነዋሪዎቿን ኑሮ የሚያሻሽሉ ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የልማት ስራዎቹ በከተማዋ አመራርና በፕሮጀክት ሠራተኞች የሌት ተቀን ትጋት በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ እምነታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ከተሞች በአረንጓዴ ውበት እና በዘመናዊ የክትመት ስርዓት ተመራጭ የአገልግሎትና ምቹ የመኖሪያ ማዕከላት እንዲሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡