ስፓርት

አትሌት ድርቤ  በግራንድ ስላም ትራክ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመች

By Mikias Ayele

December 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አትሌት ድርቤ ወልተጂ የግል የውድድር መድረክ በሆነው የግራንድ ስላም ትራክ  ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል የኮንትራት ስምምነት ፈርማለች፡፡

በስምምነቱ መሰረት በ1 ሺህ 500 ሜትር  ርቀት ላይ በመወዳደር የምትታወቀው አትሌት ድርቤ በ2025 በአሜሪካ በሚደረገው የግራንድ ስላም ትራክ ውድድር ላይ ትሳተፋለች፡፡

አትሌት ድርቤ ከፅጌ ገብረሰላማ እና ሀጎስ ገብረህይወት በመቀጠል የግራንድ ስላም ትራክ ውድድርን የተቀላቀለች ሶስተኛዋ አትሌት ሆናለች፡፡

ከስምምነቱ በኋላ አትሌት ድርቤ የግራንድ ስላም ትራክን  በመቀላቀሏ መደሰቷን ገልፃ ውድድሩን እንድትቀላቀል እድል ለፈጠሩላት አስልጣኟ ፣ ቤተሰቦቿ እና ደጋፊዎቿ ምስጋና አቅርባለች፡፡

እያንዳንዱ የአትሌቲክስ ውድድር ራሴን እንድመለከት ያደርገኛል ያለቸው አትሌቷ÷ አዲስ በሆነው የግራንድ ስላም የመካከለኛ ርቀት ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ለመወከል ጓጉቻለው ብላለች፡፡

ከድርቤ በተጨማሪ አሜሪካውያኖቹ የመሰናክል ኮከብ ቻሌብ ዲን እና ፍሬዴ ሲርቴንደን እና የ100  እና 200 ሜትር አትሌት ብሪትኔይ ብራውን በግራንድ ስላም ትራክ ለመሳተፍ ፊርማቸውን ያስቀመጡ አትሌቶች ናቸው፡፡

የግራንድ ስላም ትራክ ውድድር በቀድሞው የአሜሪካ የአጭር ርቀት ኦሎምፒክ አሸናፊ ሚካኤል ጆንሰን የተመሰረተ ሲሆን÷ በመጭው 2025 ኮከብ አትሌቶችን በማሳተፍ የመጀመሪያ ውድድሩን እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡