አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም አትሌቲክስ 25 የተለያዩ ሀገራት አትሌቶች ራሳቸውን ከማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት እንዲከላከሉ የሚያስችል የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ (ኤአይ) ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ባደረገው የአራት ዓመታት ጥናት አትሌቶቹ ለከፋ የማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸው ተገልጿል።
በመሆኑም የማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የኤአይ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
የዓለም አትሌቲክስ ባለፉት አራት ዓመታት በተደረጉ የኦሎምፒክ እና ዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ በተሳተፉ 2 ሺህ 438 አትሌቶች ላይ በማህበራዊ ትስስር ገፆች የተለጠፉ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን አስተያቶችን መርምሮ ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡
በውጤቱ መሰረት የአትሌቶችን ሰብዕና እና ስነ ልቦና የሚጎዱ አስተያይቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾች መስተዋላቸውን ገልጾ÷ ነገር ግን በቀጥታ ለአትሌቶች የተላኩ የትችትና ስድብ መልዕክቶች ለአትሌቶቹ አለመላካቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በጥናቱ መሰረት በፈረንጆቹ 2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ፣ በ2022 የኦሬገን ዓለም ሻምፒዮና፣ በ2023 የቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ በሴት አትሌቶች ላይ ፆታዊ ትንኮሳ ሲፈፀም በወንድ አትሌቶች ላይ ደግሞ የዘረኝነት ጥቃት ደርሷል፡፡
እስካሁን በተደረገው ጥናት በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ 25 አትሌቶች በማህበራዊ ትስስር ገፆች ጥቃት እንደደረሰባቸው ጠቅሶ፤ አትሌቶቹ የሚደርስባቸውን ጫና ለመቀነስ ተቋሙ የኤአይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ከ25 አትሌቶች ውስጥ የከፋ የማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት ሰለባ የሆኑት አምስት አትሌቶች ከወራት በፊት በተደረገው የፓሪሱ ኦሊምፒክ የተወዳደሩ አትሌቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡
በቀጣይም በማህበራዊ ሚዲያ በአትሌቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመለየት እና በማጥናት እንዲሁም አትሌቶችን በማማከር የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከል እንደሚሰራ የዓለም አትሌቲክስ ገልጿል፡፡