የሀገር ውስጥ ዜና

የቱርክሜኒስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ

By amele Demisew

December 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከቱርክሜኒስታን የንግድ ም/ቤትና ኢንዱስትሪ ፕሬዚዳንት መርገን ጉረዶቭ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል የቱርክሜኒስታን ባለሃብቶች በለውጥ ጎዳና ላይ በምትገኘውና የአፍሪካ መግቢያ በር በሆነችው ኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጊዜው አመቺ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች የበለጸገች መሆኗን ጠቁመው÷የሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ እየተተገበረ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በግብርናና በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በማዕድን ቁፋሮ፣ በቴክኖሎጂና ሌሎች ዘርፎች ኢትዮጵያ የቱርክሜኒስታን ባለሃብቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡

ስለሆነም የቱርክሜኒስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እዲያፈሱ አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መርገን ጉረዶቭ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በቀጣናው ካሉ ሀገራት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ተመራጭ እንደሆነች መጥቀሳቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚሰሩና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን አማራጭ እንዲገነዘቡ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡