ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርትን ባህል ማድረግ ይገባል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)የከተማው ነዋሪ በአካልና በአዕምሮ የዳበረ እንዲሁም ጤናው የተጠበቀ እንዲሆን ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርትን ባህል ማድረግ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
“ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ለሁሉአቀፍ የማህበረሰብ ጤንነት!” በሚል መሪ ሃሳብ የጤና ሚኒስቴር አመራሮች እና ሰራተኞች ከከተማው ነዋሪዎች ጋር በመሆን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አከናውነዋል።
ይህን አስመልክቶ ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ÷”የከተማችን ነዋሪ በአካልና በአዕምሮ የዳበረ እንዲሁም ጤናው የተጠበቀ እንዲሆን ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርትን ባህል በማድረግ ሁሉም በየአካባቢው እና በየመስሪያ ቤቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እንዲያደርግ መስራት ይኖርብናል” ብለዋል።
ጎዳናዎችን ጽዱ እና ለጤና ተስማሚ እንዲሆኑ ተደርገው የተገነቡ መሆናቸውን የገለፁት ከንቲባዋ “ሁላችንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እያደረግን እንንከባከባቸው” ሲሉም አስገንዝበዋል።