Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የ2024 የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች የመጨረሻ እጩዎች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2024 የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች የመጨረሻ አምስት እጩዎች ዝርዝር ይፋ ተደርጓል፡፡

የብራይተን ሆቭ አልቢዮን እና የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን የፊት መስመር ተጫዋች ሲሞን አዲንግራ ከእጩዎቹ መካከል አንዱ ነው፡፡

ተጫዋቹ ኮትዲቯር አዘጋጅታ ባሸነፈችው የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡

ሲሞን አዲንግራ ኮትዲቫር በፍጻሜው ናይጄሪያን 2 ለ 0 በረታችበትና ዋንጫውን ባነሳችበት ጨዋታ ለሁለቱም ግቦች ኳስ አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን÷የውድድሩ ምርጥ ወጣት ተጫዋች በመባል መመረጡም የሚታወስ ነው፡፡

ሌላኛው እጩ ደግሞ የ28 ዓመቱ የጊኒ ብሄራዊ ቡድንና የቦሩሺያ ዶርቱመንድ አጥቂ ሴሩህ ጉራሲ ሲሆን÷ ተጫዋቹ በቡንደስሊጋው በውድድር ዓመቱ 28 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

ለ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከጊኒ ባደረገችው ጨዋታም 3 ግቦችን በማስቆጠር ሃትሪክ መስራቱ ይታወሳል፡፡

ሞሮኳዊው አሽራፍ ሃኪሚ ሌላኛው የ2024 የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች እጩ ሲሆን÷ በክለቡ ፒኤስጂ የፍራንስ ሊግ 1 ዋንጫን ጨምሮ ሌሎች ክብሮችን ማሳካት ችሏል፡፡

ሀገሩ ሞሮኮ በፓሪሱ ኦሎምፒክ የነሃስ ሜዳልያን ስታሸንፍ የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ስኬታማ የውድድር ዓመት ማሳለፉም አይዘነጋም፡፡

የአትላንታውና የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች አዴሞላ ሉክማን ከእጩዎች መካካል ሲሆን÷ ተጫዋቹ በአትላንታ ሴሪ ኤ ስኬታማ የውድድር ዓመትን ሲያሳልፍ እንዲሁም በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ለፍጻሜ ሲደርስ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡

የማምሎዲ ሰንዳውንስ እና የደቡብ አፍሪካው ግብ ጠባቂ ሮንዌን ዊሊያምስም ከእጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ መካተቱን የካፍ መረጃ ያመላክታል፡፡

የ32 ዓመቱ የባፋና ባፋና አምበል በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ አስገራሚ ብቃቱን ያሳየ ሲሆን÷ ሀገሩ ለ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ስታልፍ የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ምርጥ የውድድር ዓመትን አሳልፏል፡፡

የ2024ቱ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች የካፍ ሽልማት መርሐ ግብር በሞሮኮ ማራካሽ በመጪው ሰኞ ይካሄዳል፡፡

Exit mobile version