አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጣዕሙ ለየት ያለው የኢትዮጵያ ቡና በቻይና ገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚስዮን መሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር ተናገሩ።
አምባሳደር ደዋኖ በቻይና ንግድ ሚኒስቴር የቻይና ቡና ኢንዱስትሪ ማህበር እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ዋንግ ቢን ከተመራ የተለያዩ የቡና ኩባንያ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም የኢትዮጵያ የቡና ምርቶች አዳዲስ ገበያ ለማፈላለግ እንዲሁም በቻይና የቡና ኩባንያዎች ዘንድ ምርቱን ይበልጥ ማስተዋወቅ በሚቻልበት መንገዶች ላይ መክረዋል።
አምባሳደር ደዋኖ በወቅቱ ÷ የኢትዮጵያ የቡና ምርት በጥራትም ሆነ በብዛት እየጨመረ መምጣቱን አስረድተው ኢትዮጵያን በቡና ምርት ግንባር ቀደም ለማድረግ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ለየት ያለ ጣዕም ስላለው በቻይና ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን የገለፁት የቻይና የቡና ኢንዱስትሪ ማህበር ዳይሬክተር ዋንግ ቢን ማህበራቸው ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ቡና ማስተዋወቂያ ፎረም ለማዘጋጀት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በሚካሄዱ የተለያዩ የቡና ፎረሞች ላይ የማህበሩ አባላት እንዲሳተፉ የሚደረግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉት በቻይና ግዙፍ እና ታዋቂ የሆኑ የቡና ዘርፍ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ቡናን በቀጥታ ከላኪዎች ለመግዛት ዝግጅት ላይ መሆናቸዉን መናገራቸውን የኤምባሲው መረጃ አመላክቷል።