Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ምክር ቤቱ የኢንቨስትመንትና የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር እይታ መራ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንቨስትመንትና የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴ መራ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባውም የኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅን እና የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ ልኳል።

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ጫላ ለሚ የኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፥ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ የስራ እድል ፈጠራ፣ የቴክኖሎጂ እና የክህሎት ሽግግር ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እንዲሁም የሀገሪቱን የተፈጥሮ፣ የባህል እና ሌሎች ሀብቶችን ጥቅም ላይ ማዋልን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማፋጠን፣ የእድገቱን ዘላቂነት ማረጋገጥ፣ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማጠናከር እና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በማለም እንደሆነም ገልፀዋል።

እንዲሁም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለማፋጠን እና በተለያዩ ዘርፎች መካከል ያለውን ትስስር ለማሳለጥ እና የውጭ ባለሀብቶች የተሳትፎ መስኮችንን ለማስፋት እንደሆነም ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ረቂቅ አዋጁ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተካሄዱ ካሉ ለውጦች ጋር እንዲናበብ ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጎለብት ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑንም አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት አስተያየት፥ በዚህ መልኩ መሻሻሉ ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ጠቃሚ ነው፤ ረቂቅ አዋጁ ከሀገሪቱ ህግ ጋር የሚጋጩ ነገሮች እንዳይኖሩት ቋሚ ኮሚቴው በጥልቀት ቢያየው የሚል ሀሳብም አቅርበዋል።

በኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጁ ውስጥ ባለሀብቶች በሚያለሙበት ጊዜ የአካባቢ ጥበቃ ላይ መስራት እንደላባቸው የሚደነግግ አንቀፅ ቢካተትም መልካም ነው ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያዩ በኋላ ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለንግድ እና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ደምጽ መርቷል።

ምክር ቤቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ስለማዛወር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ላይም ምክክር አድርጓል።

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ጫላ ለሚ፥ የአዋጁ ዋና አላማ የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት ማሻሻል፣ ተወዳዳሪነታቸውን ማጎልበትና የካፒታል አቅርቦትን እንዲሁም የመንግስት የፋይናንስ አቅርቦትን ለማጎልበት ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ ከ20 ዓመታት በላይ በማስቆጠሩ የህግ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያዩ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በመቀጠልም ምክር ቤቱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን ተመልክቷል።

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ጫላ ለሚ፥ ረቂቅ አዋጁ መንግስት ተገቢውን ታክስ መሰብሰብ እንዲችል የሚያግዝ፣ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ አስተዋፅኦ የሚያደረግ እንዲሁም የህብረተሰቡን ጤና በሚጎዱ እና የማህበራዊ ችግር በሚያስከትሉ በተጨማሪም መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው በማይቀንስ እቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ታክስ መጣል በማስፈለጉ መዘጋጀቱ ገልፀዋል።

የኤክሳይዝ ታክሱ በትክክል የቅንጦት እቃ ተብለው በተለዩ፣ በህብረተሰብ ጤና እና በአከባቢ ደህንነት ላይ ችግር የሚያስከትሉ የነዳጅ ምርቶች፣ተሽከርካሪዎችና የፕላስቲክ እቃዎች የሚጣል መሆኑንም ገልፀዋል።

የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጁ መሰረት ዝቅተኛው እስከ 10 በመቶ ሲሆን፥ ከፍተኛው ደግሞ አስከ 500 በመቶ መሆኑም ተገልጿል።

በዚህም መሰረት 10 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ከሚጣልባቸው ውስጥ የፊቶ ግራፍ እና የቪዲዮ ካሜራዎች፣ የቲቪ መቀበያ እና መሰል የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ይገኙበታል።

ከ400 እስከ 500 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ከሚጣልባቸው ውስጥ በአብዛኛው በአውሮፓውያኑ ከ2012 በፊት ማለትም 7 ዓመትና ከዚያ በላይ በሆናቸው ተሽከርካሪዎች መሆናቸውም ተነግሯል።

የትራክተር ምርቶችም እንደ አገልግሎት ዘመናቸው ማለትም 4 ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆናቸው ላይ ከ100 እስከ 400 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ የሚጣል መሆኑም በረቂቅ አዋጁ ተመልክቷል።

በሀገር ውስጥ ተገጣጥመው ለገበያ የሚቀርቡ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ደግሞ 30 በመቶ መሆኑም ተደንግጓል።

ከዚህ በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ የአልኮል መጠጦች፣ የትምባሆ ምርቶች፣ ጣፋጭና ጨዋማ ምግቦች፣ ስባማ ምግቦች ላይ እንዲሁም የተሰፉ ልብሶች ላይ የታሸጉ እና ጋዝ ያላቸው ውሃዎች ላይ ታክስ እንዲጣል የሚያዝ መሆኑን ታውቋል።

የምክር ቤቱ አባላት ከታክሱ ዓላማ አንጻር እንደ ስኳር፣ ዘይት እና ጨው ላይ ታክስ መጣሉ ከዝህብ ጥቅም ጋር እንዳይጋጭ መመልከት ተገቢ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የግብርና መሳሪያ የሆኑ ትራክተሮች ላይ ከአገልግለት ዘመናቸው አንጻር ጉዳት ቢያደርሱም እንኳ ምርቶቺ ሊበረታቱ ሲገባ ታክስ መጣሉ አግባብነት አንደሌለውም አንስተዋል።

ምክረ ቤቱ ዛሬ በነበረው መደበኛ ስብሰባው የኤክሳይዝ ረቂቅ አዋጅ ሰዎች ከሚጠቀሙባቸው የቅንጦ እቃዎች ላይ ገቢ በመሰብሰብ በድህነት ለሚገኙ ዜጎች ለመደጎም እንደሚያስቸል አምኖበታል።

በመጨረሻም የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

Exit mobile version