ኮሮናቫይረስ

በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ፍጥነት አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል-የዓለም ጤና ድርጅት

By Tibebu Kebede

July 21, 2020

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ፍጥነት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

የዓለም ጤና ድርጅት በትናንትናው እለት እንዳስታወቀው በተለይም በደቡብ አፍሪካ እየታየ ያለው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት መጨመር ፤ በሌሎች አፍሪካ ሀገራትም ሊከሰት እንደሚችል ማሳያ ነው ብሏል።

ዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ ህክምናዎች ዳይሬክተር ዶክተር ማይክ ረያን በሰጡት ማብራሪያ፥ በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ስርጭት ፍጥነት እየጨመረ የመጣበት ጊዜ ላይ በመሆኑን በመጥቀስ፤ ይህም እንደሚያሰጋቸው ነው ያስታወቁት።

እስከ ቅርብ ጊዜ በአፍሪካ ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር ሲነፃፀር እምብዛም እንዳልነበረ ነው የገለፁት።

በአፍሪካ እስካሁን 725 ሺህ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፥ 15 ሺህ ሰዎችም ህይወታቸው አልፏል፤ ይህም አፍሪካ በዓለም ላይ በቫይረሱ ዝቅተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ክፍለ አህጉሮች ከኦሽኒያ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቫይረሱ ስርጭት አስጊ በሆነ ፍጥነት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፥ በተለይም በደቡብ አፍሪካ ያለው ስርጭትን እንደማሳያነት መነሳት ይችላል።

በደቡብ አፍሪካ ባሳለፍነው ቅዳሜ ብቻ በአንድ ቀን በ13 ሺህ 373 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይሰር የተገኘ ሲሆን፥ ይህም በዓለም ላይ በአንድ ቀን ከፍትኛ ቁጥር ካስመዘገቡ ሀገራት 4ኛ ደረጃን ያየዘ መሆኑ ተገልጿል።

በሀገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ350 ሺህ የበለጠ ሲሆን፥ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ5 ሺህ አልፏል፤ ይህም በአፍሪካ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑም ነው የተመላከተው።

ዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ ህክምናዎች ዳይሬክተር ዶክተር ማይክ ረያን፥ ደቡብ አፍሪካ እያስተናገደች ያለው ክስተት በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊደገም ስለሚችል እንደማስጠንቀቂያ መመልከት ይገባል ብለዋል።

ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ቀደም ብሎ ቫይረሱ በደቡብ አፍሪካ መከሰቱን የሚናገሩት ዶክተር ማይክ ራያን፥ ቫይረሱ መጀመሪያ ሀብታም ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ ላይ በስፋት እንደነበረ እና አሁን ላይ ግን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ወደሚገኙ ዜጎች መንደር እንዲሁም ወደ ገጠራማ አካባቢዎች እየተዛመተ እንደመጣም ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም ባሳለፍነው ሳምንት በሀገሪቱ ያለው የስርጭት መጠን በ30 በመቶ ብቻ እንደጨመረም አመላክተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት የቫይረሱ ስርጭት በኬንያ በ31 በመቶ፣ በማዳካስካር በ50 በመቶ፣ በዛምቢያ በ57 በመቶ እንዲሁም በናሚቢያ በ69 በመቶ መጨመሩንም አስታውቅዋል።

አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ ምደር ላይ በከፍተኛ ፍጥነት የሚሰራጭበትን ጊዜ መመልከት እየጀመርን ነው ያሉት ዶክተር ማይክ ራያን፤ “ይህ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የማንቂያ ደውል ሊሆን ይገባል” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

ምንጭ፦ aljazeera.com

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።