Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

1 ሺህ 443 ኢትዮጵያውያን እስረኞች ከታንዛኒያ ወደ ሀገር ቤት ሊመለሱ ነው

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 7፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 443 ኢትዮጵያውያን እስረኞች ከታንዛኒያ ወደ ሀገር ቤት ሊመለሱ መሆኑን በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

ኤምባሲው መቀመጫውን በታንዛኒያ ካደረገው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ልኡክ እንዲሁም ከአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ነውኢትዮጵያውያኑን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው የሚመልሰው።

በዚህ መሰረትም በታንዛኒያ እስር ቤቶች የነበሩ 1 ሺህ 443 ኢትዮጵያውያንን በማስፈታት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ዝግጅት መጠናቀቁን ኤምባሲው ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት እና የአውሮፓ ህብረት ለዚህ የሚያስፈልገውን ሙሉ ወጪ በጋራ በመሸፈን የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የታንዛኒያ ቢሮ ጋር በመተባባር ኢትዮጵያዊያኑን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተመላክቷል።

ከስምምነት ላይ የተደረሰውም በታንዛኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ፣ በታንዛኒያ ከአውሮፓ ህብረት ልኡክ አምባሳደር ማንፈሬድ ፋንቲ ፣ የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የታንዛኒያ ቢሮ ተጠሪ ዶክተር ቃሲም ሱፊ እና በታንዛኒያ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ልኡክ ፕሮግራም ኦፊሰር ሳቲኔ ሄልዴክጃኤር ጋር ባደረጉት ውይይት መሆኑ ተገልጿል።

Exit mobile version