የሀገር ውስጥ ዜና

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከሚሠሩ የተመድ ኤጀንሲዎች ጋር ተወያዩ

By ዮሐንስ ደርበው

December 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የተመድ ዋና ተጠሪና የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ እና በኢትዮጵያ ከሚሠሩ የተመድ ኤጀንሲዎች ጋር በባለብዙ ዘርፎች የትብብር መስክ ዙሪያ ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ተመድ መሥራችነቷ ድርጅቱ መርሆቹን ተከትሎ ተልዕኮዎችን እንዲሳካ ቀጣይነት ባለው መንገድ በንቃት የምትንቀሳቀስ ሀገር መሆኗን ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት ያስቀመጣቸውን ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች መሠረት በማድረግም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የድርጅቱ ድጋፍ ከሀገሪቱ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጋር ተናበው መከናወናቸው ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሕይወት በማሻሻል ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተመድ የተቀመጡ ዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በምታደርገው ጥረት÷ በድርጅቱ ጥላ ሥር የሚገኙ ኤጄንሲዎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የተመድ ዋና ተጠሪና የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አልካባሮቭ  (ዶ/ር) እና የተመድ ኤጄንሲዎች ተወካዮች በኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት በሰጣቸው መስኮች ዙሪያ ተባብሮ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።