Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሕብረቱ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ተወካይ ጀስላይን ናሂማ ገለጹ።

በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንና በአፍሪካ ሕብረት ትብብር ከየቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ቋቋምና ወደ ማህበረሰቡ የመመለስ የስራ አፈጻጸም የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን÷ መድረኩም የቀድሞ ተዋጊዎችን በተሀድሶ ስልጠና ወደ ማህበረሰባቸው ለመቀላቀል በሚደረገው ጥረት ስኬቶችን በማስቀጠል ውስንነቶችን ለማረም ገንቢ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የተሀድሶ ማዕከላትን የቅበላ አቅም ማሳደግ፣ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ የሃብት ምንጮችን ማሰባሰብና የመልሶ ማቋቋም ሂደትን ማሳለጥ በትኩረት የሚሰራባቸው ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተባባሪ ተቋማት በሚያደርጉት ዕገዛም ከመቐለና ዕዳጋ-ሀሙስ ማዕከላት በተጨማሪ ሌሎች ማዕከላትን በማስጀመር 75 ሺህ የትግራይ ክልልን የቀድሞ ታጣቂዎች እስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ ለማሰልጠን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ተወካይ ጀስላይን ናሂማና በበኩላቸው÷ ለሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች የሚደረጉ ድጋፎች በአጀንዳ 2063 ሰላማዊና የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ የማቋቋም ስራ ትጥቅ ከማውረድና ወደ ማህበረሰቡ ከመቀላቀል ባሻገር አምራች ዜጋ የሚያደርግ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በፕሪቶሪያው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ማዕቀፍ መሰረት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

Exit mobile version