Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሳዑዲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ተጠየቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አርጋ ከሳዑዲ አረቢያ ንግድ ምክር ቤት ሃላፊዎች ጋር የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ይበልጥ ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ፥ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የኢኮኖሚ ዘርፍን ጨምሮ የኢትዮጵያ ጠንካራ ስትራተጂክ አጋር ነው።

ኢኮኖሚያዊ ትብብሩን ይበልጥ ለማጎልበት የሳዑዲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስመንት ተሳትፎ እንዲያሳድጉ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሰኔ ወር በሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን የተመራ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉን አስታውሰው ፥ ጉብኝቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።

የሳዑዲ አረቢያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀሰን አል-ሁዌይዚ ፥ በኢትዮጵያ ያለንን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት አድርገናል ብለዋል።

የንግድ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት ስምምነት የደረሰባቸውን ጉዳዮች ወደ ውጤት በመቀየር ረገድ የተሻለ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶት የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አብደላ አል-አጅሚ በበኩላቸው ፥ የሳዑዲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ኢንቨስትመንት እንዲያሳድጉ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለባለሃብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀው ፥ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በቅርበት መፍታት እንደሚጠበቅበት ማመላከታቸውን የሳዑዲ አረቢያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Exit mobile version