አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ቴሌኮሙኒኬሽን ግሩፕ የሥራ ኃላፊዎች የተመራ ልዑክ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚገኘውን የኤክስፒሪየንስ ማዕከል ጎበኘ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋማቸውን የቴክኖሎጂ ሂደት ጨምሮ አሁን እስከደረሰበት ስማርት ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ማዕድን ልማት፣ ስማርት ቱሪዝም የመሳሰሉ የዲጂታል ሶሉሽኖችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የልዑኩ አባላት በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም ለዲጂታል ሶሉሽኖች የሰጠውን ትኩረት እና የገነባውን የመሠረተ-ልማት አቅም አድንቀው፤ ተቋሙ ለበርካታ የአፍሪካ ኦፕሬተሮች አርዓያ መሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የኤክስፒሪየንስ ማዕከሉ ፈጠራን በማጎልበት እና የዲጂታል ሥነ-ምኅዳሩን በማሳደግ በአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ ጉልህ ዐሻራውን ማሳረፍ እንደሚችል መገለጹን የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ያመላክታል፡፡