አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የ19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ብዝኃነት ለሀገራዊ መግባባትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መሠረት ነው ብለዋል።
ለሰው ልጅ መሠረቱ አብሮነት ነው፤ ሀገርም ይገነባል ለዚህም ደግሞ መግባባት መነጋገርና መረዳዳትን ይጠይቃል በማለት ገልጸዋል።
ሕብረ-ብሔራዊነት በሚስተናገዱባት ኢትዮጵያ ነጠላ ትርክት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፤ የለውጡ መንግሥት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ በውይይት የወል ትርክት ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ብዝኃ ማንነት የሚከበርበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የድርሻውን መወጣቱን ተናግረዋል።
በክልሉ ፅንፈኝነት የፈጠረው ችግር በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ጠቅሰዋል።
መንግሥት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ጫካ የገቡ ልጆቻችንና ወንድሞቻችን በሰላም ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በሙሉጌታ ደሴ